Psalms 77

የእስራኤል ጥንተ ነገር አሰላስሎ

ለመዘምራን አለቃ፤ ለኤዶታም፤ የአሳፍ መዝሙር።

1ድምፄን ከፍ አድርጌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፤
ይሰማኝም ዘንድ ወደ አምላክ ጮኽሁ።
2በመከራዬ ቀን እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤
በሌሊትም ያለ ድካም እጆቼን ዘረጋሁ፤
ነፍሴም አልጽናና አለች።

3አምላክ ሆይ፤ አንተን ባሰብሁ ቍጥር ቃተትሁ፤
ባወጣሁ ባወረድሁም መጠን መንፈሴ ዛለች። ሴላ
4ዐይኖቼ እንዳይከደኑ ያዝሃቸው፤
መናገር እስኪሳነኝ ድረስ ታወክሁ።
5የድሮውን ዘመን አሰብሁ፤
የጥንቶቹን ዓመታት አውጠነጠንሁ።
6ዝማሬዬን በሌሊት አስታወስሁ፤
ከልቤም ጋር ተጫወትሁ፤ መንፈሴም ተነቃቅቶ እንዲህ ሲል ጠየቀ፦

7“ለመሆኑ፣ ጌታ ለዘላለም ይጥላልን?
ከእንግዲህስ ከቶ በጎነትን አያሳይምን?
8ምሕረቱስ ለዘላለም ጠፋን?
የገባውስ ቃል እስከ ወዲያኛው ተሻረን?
9እግዚአብሔር ቸርነቱን ዘነጋ?
ወይስ ከቍጣው የተነሣ ርኅራኄውን ነፈገ?” ሴላ

10እኔም፣ “የልዑል ቀኝ እጅ እንደ ተለወጠ ማሰቤ፣
ይህ ድካሜ ነው” አልሁ።
11 የእግዚአብሔርን ሥራ አስታውሳለሁ፤
የጥንት ታምራትህን በርግጥ አስታውሳለሁ፤
12ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፤
ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ።

13አምላክ ሆይ፤ መንገድህ ቅዱስ ነው፤
እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው?
14ታምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ነህ፤
በሕዝቦችም መካከል ኀይልህን ትገልጣለህ።
15የያዕቆብንና የዮሴፍን ልጆች፣
ሕዝብህን በክንድህ ተቤዠሃቸው። ሴላ

16አምላክ ሆይ፤ ውሆች አዩህ፤
ውሆች አንተን አይተው ተሸማቀቁ፤
ጥልቆችም ተነዋወጡ።
17ደመናት ውሃን አንጠባጠቡ፤
ሰማያት አንጐደጐዱ፤
ፍላጾችህም ዙሪያውን አብለጨለጩ።
18የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ተሰማ፤
መብረቅህ ዓለምን አበራው፤
ምድርም ራደች፤ ተንቀጠቀጠች።
19መንገድህ በባሕር ውስጥ ነው፤
መሄጃህም በታላቅ ውሃ ውስጥ ነው፤
ዱካህ ግን አልታወቀም።

20በሙሴና በአሮን እጅ፣
ሕዝብህን እንደ በግ መንጋ መራኸው።
Copyright information for AmhNASV